ማድጋ ፍለጋ

(አግማስ የኛሰው)

  

         ይህ ልቦለድ አይደለም። አንድ ከቶሮንቶ ወደ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ ሔዶ ገበሬ የሆነ ኢትዮጵያዊ ገጠመኝ ነው።

      ከጎንደር ከተማ ወደ ባህዳር የሚወስደው መንገድ አዘዞን፣ ጠዳን፣ ባሕር ግምቢን አልፎ ማክሰኚት ይደርሳል። የማክሰኚት የቅዳሜ ገበያ በጠዋቱ የሚጀመረው በገበሬዎች ነው። ገበሬዎች በጠዋቱ የጅምላ ሸቀጣቸውን ለቸርቻሪና ለአከፋፋይ ለመሸጥ ከአቅራቢያ መንደሮች ከግራርጌ፣ ከዶጎማ፣ ከጋአፊ፣ ከጀጃ፣ ከእንፍራንዝ፣  እና ከመሳሰሉት ማሳቸው ያፈራውን በትከሻቸው፣ በአህያ ጀርባ፣ ሴቶቹም አናታቸው ላይ ቁጭ አርገውና ተሸክመው ማክሰኚት ገበያ ይታደማሉ።  

       ማክሰኚት የምትደምቀው ረፈድፈድ አድርጋ ቢሆንም እኔ ግን ማሳዬ ከሚገኝበት ከፈንጠር ወደ ማክሰኚት የሔድኩት ማልጄ ነው። ጠዳ ከተማ ከሚቆሙት ሚኒባሶች አንዱ ውስጥ ገባሁ። ሚኒባሱ ቦሎው የሚፈቅድለት 12 ሰው ብቻ ቢሆንም 23 ሆነን ተጭነን ቄስ ድባን ለቀቅን። ቄስ ድባ ዛሬ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የግብርና ዲፓርትመንት ቢሰራበትም ጥንት ግን የጣዲቁ ዮሐንስ አፅም ወደ የትም አይሔድም ብለው ቄሶች የተደባደቡበት ቦታ ስለሆነ የቀዬው ሰው ቄስ ድባ ይለዋል። እንግዲህ ቄስ ድባ የጠዳ ከተማ መውጫ ነው።

         ጀማሪ ገበሬ ነኝና የዘር ሽንኩርት ልገዛ እኔጋ የሚሰራውን አውራጃው ከተባለው ገበሬ ጋር ገበሬዎቹ ገበያ የሚቆሙት ላይ ዳገት መጨረሻ ነውና ወደዛው አመራን። አውራጃው “የዶጎማ ሽንኩርት ያለው!” እያለ እየተጣራ ስንወጣ አንድ አዛውንት “ወድህ ኑ” አሉን። በአካባቢው አጠራር 3 ኬሻ፣ወይንም ሶስት ማዳበሪያ ሀገሬ ሽንኩርት ከፊታቸው አስቀምጠዋል። በጃቸው ጠፍር የያዙ ስሆን የጠፈሩ ሌላኛው ጫፍ ከገበሬው ኋላ ሶስት ሜትር ራቅ ብለው የቆሙት አህዮች አንገት ላይ ታስሯል።

           አዛውንቱ ፊታቸው ላይ የዕድሜያቸው ታሪክ የተፃፈባቸው ብዙ መስመሮች ተጋድመዋል። መስመሮቹ ወፋፍራምም ቀጫጭንም ሲሆኑ አንዳንዶች ተጨማደዋል። ሰውየው አዛውንት ስለሆኑ አዝመራው አንተ ሲላቸው ቅር ብሎኛል። ግን በጎንደር አንቱ የሚባል የለም። አዛውንት ወንዱ ባባ፣ ሴቷ ታታዬ ነው የሚባሉ። አንድ የሚኒባስ ረዳት አሮጊቷን ታታዬ እዚህ ቁጭ በይ ቢላት አለማክበሩ አይደለም በቃ ጎንደር አንቱ አይሉም።

          “ የደጎማ ነው?”  አለ አውራጃው ሀገሬ ሽንኩርቱን ከኬሻው አፍ ላይ ዘገን አርጎ። በጎንደር ሶስት ሽንኩርቶች በጣም ታዋቂ ናቸው። አንደኛ ነጭ ሽንኩርት፣
 
ሁለተኛ በሰል የሚሉት ወይንጠጅማ  ቀለም ያለው በቶሮንቶ ሬድ ኦኒየን የሚባለው የፈረንጅ ሽንኩርትን ነው።

ሦስተኛው እኔ ላለማ ያሰብኩት ሀገሬ ሽንኩርት ሲሆን በሌላ አካባቢ የሐበሻ ሽንኩርት የሚባለው ወይንም እዚህ ቶሮንቶ ሾላት የሚባለው ማለት ነው።

                   “ለምን ብዬ እዋሻለሁ?” መለሰ ገበሬው። ዶግማ የበለሳን መንገድ ይዘው ሲኬድ ጋራው ጫፍ ላይ የሚገኝ ቦታ ሲሆን የዶጎማ ሽንኩርት ለኔ ማሳ አፈር ተስማሚ ነው።  በኪሎ ስንት ነው አልኩ ገበሬውን። በኪሎ አልሸጥም በማድጋ ነው አለ። ከግብርና ባለሙያዎች እንደተነገረኝ አንድ ማድጋ 30 ኪሎ ነው። ስንት ማድጋ ይሆናል ስለው ሶስቱ ሶስት ማድጋ አለ ።
     
             ማድጋው ስንት መሆኑ ነው አለ አውራጃው 300 አለ  ገበሬው።  ገበሬው ማድጋ ይዞ ስላልመጣ በኪሎ 12.50 ተስማምተን ሲመዘን አንዱ ኬሻ 18 ኪሎ ሆነ። ሌላኛው 22 ሶስተኛው ደግሞ 23 ሆነ። ገበሬው 90 ኪሎ ብሎ ይዞ የመጣው ሀገሬ ሽንኩርት ሁለት ማድጋ ብቻ መሆኑን ሲሰማ እነዛ የተጣጠፉት የአዛውንቱ የፊት መስመሮች በኃዘን ተንጠለጠሉ።

           የጎንደር ገበሬ ሁሉ ሲገበያይ በማድጋ ነው። ያረሰውን የሚለካው በማድጋ ነው፣ ተስፋው በማድጋ የተለካ ነው። ገንዘብ ሲቀበል ግን በኪሎ ነው። ለገበሬ ው15 ብር ሒሳብ ገዝቼው ደምሬ የሰጠሁትም እኔ ነኝ። ገበሬው ታጥቦ የማያውቅ የሚመስለውን መዳፉን ዘርግቶ የሰጠሁትን ሲቀበል ሀዘን አንጀቴን በላው። ድካሙን በትክክል እንዳገኘ ማረጋገጫ እንኳን የለውም። ምንምንኳ አትርፌ ብሰጠውም። ገበሬው ጭንቅላት ውስጥ ድካሙ አልተሰላምና አሳዘነኝ። 

               ከዚያን ቀን ጀምሮ ማድጋ ፍለጋ ብርሃላ ሔድኩ። የብርኃላ ገበሬዎቹ ዳጉሳም ሆነ የፈረንጅ ማሽላ (በቆሎ በአካባቢው የፈረንጅ ማሽላ ነው የሚባለው) አምርተው ስንት አመረታችሁ ብትሏቸው 10 ማድጋ ሊሏችሁ ይችላሉ። ግን በድፍን ብርኋላ አንድም ገበሬ ማድጋ የለውም፣ በጋአፊም እንደዛው በማድጋ እያሰቡ ማድጋ ግን አይተው አያውቁም። ግብርና ቢሮ ሐጄ ማድጋ አይተው እንደሆነ ጠየኩ። አንድ 25 ዓመት በግብርና ያገለገለ ባለሙያ በረትጌ ወሰደኝ። በረትጌዎች ጭራሹኑ ማድጋ አይተው አያውቁም። ማጫ ሔድን የለም። አሥሩም ቀበሌ ማድጋ አላዩም ድሮ ነበረ አሁን የለም። ግን ዛሬም ድረስ እያንዳንዱ ገበሬ በማድጋ ነው የሚለካው።

                 አምባዬ አድማሴ የ74 ዓመት ገበሬ ነው። የስንዴ ማሳው ላይ ሕጅ ስያደርግ ደርሼበት “ና አግማስ ብላ” ብሎኝ የዳጉሳ እንጀራ እና የክክ ወጥ አጣብቀን እየበላን አሁን ስንዴው ስንት ኪሎ ይህናል? አልኩት ከፀሐዩ ለመከላከል የያዘልኝን ዣንጥላ ልቀበለው ስል አንተ እንግዳ ነህ ዣንጥላ አትይዝም ብሎ እየተከላከለ የዳጉሳ እንጀራውን ጠቅልሎ “ አዪ ጋሼ የከተማ ሰው ነው በሚዛን የሚለካ እኛ በማድጋ ነው የምንለካ” አለኝ

                   ምሳውን እንደጨረስን ከወደጥግ በኬሻ ተሰፍሮ የተቀመጠውን እያሳየ “ያውልህ ያ አንድ ማድጋ ነው።” አለኝ። ለክተኸዋል? ስለው “ሳልሰፍርማ ለምን አስገብቼው?” ሲለኝ ስንዴውን እዛው ውድማ ላይ ዘረገፍኩና እስኪ በማድጋ ለካልኝ አልኩት። በጣሳ መስፈር ሲጀምር በጣሳ አይደለም በማድጋ ለካልኝ አልኩት። የ74 አመት ገበሬ ማድጋ እንደሌለው ያወቀው ያን ቀን ነው። ኸረግ ከየት አምጥቸው ነው በማድጋ ለካሁት ያልኩ? አንተ ሰው እንጃ ገና ግብርና ሳታስተምረን የምትቀር አይደለህም አለኝ።

                ገበሬው በጠቅላላ በሌለ ማድጋ እየለካ እንዳለ ያስባል። እንዴት እንደምረዳቸው አላውቅም። በኪሎ ሲሸጡም አይቻለሁ ኪሎ አያውቁም። መዛኞች ከገዢዎች ተስማምተው ሲያታልሏቸው ብዙ ግዜ አይቻለሁ። በጣሳ ብቻ ነው በትክክል የሚለኩት። በጅምላ ገዢ ግን በጣሳ ስለማይገዛ ገበሬው አመረትኩ ከሚለው የግማሹን ገንዘብ ይዞ ቤቱ ይገባል ኦ የሀገሬ ገበሬ አንጀቴን በላው፡

  

ማክሰኚት ገበያ


  
መገጭ የነጭ ሽንኩርት   እርሻ ፕሮጀክት
  





OUR FACES
  1. ሕጃ
    ሕጃ
    በጠዳ ውድማ ሲጣል ከብቶች ያበራያሉ። በአካባቢው ሕጃ ተብሎ ይጠራል
  2. የጠዳ ወጣቶች
    የጠዳ ወጣቶች
    መገጭ ወንዝጋ አባ አስማረ ዓለሙ እርሻ አጠገብ
  3. አዝመራና መታድል
    አዝመራና መታድል
    የብርኃላ ነዋሪዎች ሲሆኑ አባትና ልጅ ናቸው።